ቀጥታ፡

የቤልጂየም እና የሉክሰምበርግ የንግድ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ በርካታ ኩባንያዎችን ያቀፈ የቤልጂየም እና የሉክሰምበርግ የንግድ ልዑክ በግንቦት ወር 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርግ ተገለጸ።

ጉብኝቱ ኩባንያዎቹ በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት በትብብር መስራት የሚችሉባቸውን አማራጮች ለመመልከት እንደሆነም ተመላክቷል።

በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የቤልጂየም-ሉክሰምበርግ- አፍሪካ- ካሪቢያን-ፓሲፊክ የኢንዱስትሪ እና ግብርና ምክር ቤት(CBL-ACP) የጋራ አዘጋጅነት የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትውውቅ ሁነት በብራሰልስ ተካሂዷል።


 

የማስተዋወቂያ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ከግንቦት 24 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት ለሚያደርጉ የቤልጂየም እና የሉክሰምበርግ ኩባንያዎች ልዑክ ነው።

በዝግጅቱ ላይ በቤኔሉክስ ሀገራት(ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ እና ሉክሰምበርግ) የሚገኙ ከ40 በላይ ኩባንያዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ፣ የአዲስ አበባ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካዮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በቤኔሉክስ ሀገራት(ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ እና ሉክሰምበርግ) እና የአውሮፓ ህብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን የኢትዮጵያ የገበያ አቅም እና አማራጭን አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።


 

የቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ የንግድ ተዋንያን በኢትዮጵያ በግብርና፣ በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በፋርማሲዩቲካል፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እንዲሁም በኢንፎርሜሽን እና ኮሙኒኬሽንስ ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ዘርፍ ያሉ እድሎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚሹ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።

በሁነቱ ላይ በኢትዮጵያ የቤልጂየም አምባሳደር አኔሊስ ቬርስቲቼል እና በኢትዮጵያ የሉክስመብርግ አምባሳደር ጂን ክራውሰር በበይነ መረብ ተሳትፈዋል።

አምባሳደሮቹ ባስተላለፉት መልዕክት በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት መስክ መሳተፍ አዋጭ እና አትራፊ መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀገራቸው መንግስታት ለባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።

የቤልጂየም-ሉክሰምበርግ- አፍሪካ-ካሪቢያን-ፓሲፊክ የኢንዱስትሪ እና ግብርና ምክር ቤት(CBL-ACP) ምክትል ፕሬዝዳንት ዶምኒክ ቪያን ምክር ቤቱ ከኢትዮጵያ ጋረ በቅርበት እንደሚሰራ እና የንግድ ልዑኩ ስኬታማ ቆይታ እንዲኖረው ድጋፍ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በኢንቨስትመንት እና ንግድ ማስተዋወቂያ መድረኩ የቤልጂየም እና ሉክሰምበርግ የንግድ ልዑክ በኢትዮጵያ የሚኖረውን ቆይታ የተመለከተ ውይይት መደረጉንም በብራሰልስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም