ጤናማ ትውልድ በመገንባት የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የትምባሆ ቁጥጥርን ማጠናከር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ጤናማ ትውልድ በመገንባት የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የትምባሆ ቁጥጥርን ማጠናከር ይገባል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 26/2017(ኢዜአ)፦ ጤናማ ትውልድ በመገንባት የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ የትምባሆ ቁጥጥርን ማጠናከር እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በዓለም ጤና ድርጅት ትብብር የተደረገው የ2024 የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ጥናት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ጥናቱ በኢትዮጵያ የትንባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር እ.አ.አ 2016 ከነበረበት 5 በመቶ ወደ 4 ነጥብ 6 ዝቅ ማለቱን አመላክቷል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ የሀገርን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ጤናማ ትውልድ መገንባት ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
እነዚህን የልማት ተግባራት ለማስቀጠል በአካል የጠናከረ እና በአዕምሮው የዳበረ ትውልድ መገንባት እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትምባሆ በጤና፣ በማህበራዊ እና በአካባቢ እያደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ የሚያስችል ቁጥጥርን ለማጠናከር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ማውጣቱን አውስተዋል።
አዋጁ መተግበር ከጀመረ ወዲህ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ የአዋቂዎች የትምባሆ አጠቃቀም ቁጥጥርን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ህጎችን በአግባቡ ተፈጻሚ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ለትምባሆ ተጋላጭ ያልሆነ ወጣት ትውልድ ማፍራት የሀገርን ብልፅግና እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም መሆኑን ጠቅሰው፥ ቋሚ ኮሚቴው የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አንስተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው፤ ትምባሆ ተላላፊ አና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ዋና መንስኤ ነው ብለዋል፡፡
ትምባሆ መጠቀም ከጤና ጠንቅነቱ ባሻገር ለኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ እንደሚዳርግ ገልጸው፤ ጥናቱ ለእነዚህ ችግሮች በመረጃ ላይ የተመሰረተ መፍትሔ ለመስጠት ግብዓት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም አዋጁን ተከትለው የወጡ ህጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድህኒት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ፥ አዋጁ ያስቀመጣቸው ክልከላዎች ተፈጻሚ በመሆናቸው የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥርና የሚያደርሰው ጫና መቀነሱን ገልጸዋል።
በቀጣይም በህግ የተደነገጉ ክልከላዎችን አጠናክሮ በመተግበር ለውጤታማነቱ ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ሃይሉ(ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አጠባበቅን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ ትውልዱ ለትምባሆ ሰለባ እንዳይሆን የጋራ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።