ቀጥታ፡

የመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ብዝኃ የልማት አቅሞችን ጥቅም ላይ በማዋል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እንዲገነባ አስችሏል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የተገበረችው የመደመር እሳቤ ሀገራዊ ብዝኃ የልማት አቅሞችን ጥቅም ላይ በማዋል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጉባኤው መክፈቻ እንደገለጹት፤ አፍሪካ ራሷን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ለነፃነትና ለእኩልነት ታግላለች።

ይህ ትግል በታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ውጤት ማምጣቱን ገልፀው፤ ለአፍሪካ ህብረት መመስረትም መነሻ እንደነበር አስታውሰዋል።


 

የአፍሪካ አባቶች ለነፃነትና ለእኩልነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ በጥበብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ልማትና ሰላም በማስመዝገብ ሊደግመው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ወጣት አመራር አባላት ተለዋዋጭ ለሆነው የዓለም ጂኦ-ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የሚመጥን ሀሳብ ማፍለቅና ውሳኔ መስጠት እንደሚጠበቅባቸው ጠቅሰዋል።

ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት ትብብርና በጋራ መስራት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ ውጤታማ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።

እሳቤው ሀገር በቀል ዕውቀቶችንና አመለካከቶችን ለማህበረሰብ ለውጥ መጠቀምን ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል።

የመደመር እሳቤ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ እሳቤው ሀገራዊ ብዝኃ የልማት አቅሞችን ጥቅም ላይ በማዋል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

የአፍሪካን ሁለንተናዊ እድገት ለማስቀጠል ወጣቱ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

በአፍሪካ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚን ለመገንባት፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትን ለማስፋፋት በትብብር መስራት እንደሚገባ በማንሳት።

በአሁኑ ወቅት በአህጉሪቱ የሚስተዋሉትን የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሌሎች ችግሮችን ወጣቱ ሊያሸንፋቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በትምህርት ጥራት፣ በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የአህጉሪቱ መሪዎች የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ድርጅቶች የተቀናጀ ድጋፍና ትብብር ማድረግ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያውያን ስታርታፖች ያስተዋወቁትን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም