በንጥረ-ነገር የበለፀገና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በንጥረ-ነገር የበለፀገና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ባህርዳር፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ በንጥረ-ነገር ይዘቱ የበለፀገና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።
በስርዓተ-ምግብ ስትራቴጂ ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀሚድ ጀማል(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የስርዓተ-ምግብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
በዚህም አርሶ አደሩ ምርትን በብዛትና በዓይነት ከማሳደግ ባሻገር አሰባጥሮ በመዝራት የስርዓተ ምግብ ችግርን መፍታት ቁልፍ ተግባር ተደርጎ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም በንጥረ-ነገር ይዘቱ የበለፀገና ደህንነቱ የተጠበቀ የምግብ አቅርቦት ለሁሉም ህብረተሰብ ተደራሽ በሚያደርግ አግባብ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ማሳካት የሚያስችል ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመው፤ የምርት ብክነትን በማስወገድና ለገበያ የሚውል ምርትን በጥራት በማምረት ላይ አተኩሮ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዚህ መድረክ ዓላማም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስትራቴጂውን በውል ተገንዝበው ለተግባራዊነቱ እንዲረባረቡ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው፤ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የስርዓተ ምግብ ችግርን መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የሰብልም ሆነ የእንስሳት ምርት ያለው አቅርቦት ከፍተኛ ቢሆንም በህጻናት ላይ የሚስተዋለው የመቀጨጭና የመቀንጨር ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የዚህ ዋና ምክንያትም ህብረተሰቡ የተመጣጠነ ምግብ የመመገብ ግንዛቤ ክፍተት የመጣ ችግር መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለመፍታት እንደመሰራ ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልልና የፌዴራል የግብርናው ዘርፍ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።