የቡና ምርታማነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ይሰራል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ምርታማነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ይሰራል - ባለስልጣኑ
ሀዋሳ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- የቡና ምርታማነትንና ጥራትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ ከቡና አብቃይ ክልሎች ለተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች የቡና ጥራትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችል የአሰልጣኞች ስልጠና በሀዋሳ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
በወቅቱ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሶፊሳ አባቡ እንዳሉት የቡናን ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የቡና ልማት ፓኬጅ መተግበሩን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ለጥራቱ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለተግባራዊነቱም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሲዳማ ክልል ቡናና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው በክልሉ 171 ሺህ ሄክታር መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ማሳም 144 ሺህ ሄክታሩ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዚህም በክልሉ በሚገኙ አስራ አምስት ቡና አብቃይ ወረዳዎቸ 195 ኩታ ገጠም ማሳ ተለይቶ 42 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።
በክልሉ የቡና ጥራትን በማስጠበቅ ወደ ማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው ቡና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝና እስከአሁን የተላከው ቡና አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ያገኘ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አምና ለ'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' ቀርበው ምርጥ አርባ ደረጃ ካገኘው ቡና ውስጥ 34ቱ የሲዳማ ቡና መሆናቸውን ጠቁመው ይህን ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለሁለት ቀን በሚቆየው ስልጠና ላይ ቡና አብቃይ ከሆኑ ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።