ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት አላት - አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡-  ኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር ያላትን የንግድ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት እንደምትፈልግ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሃኪም ሙሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የቦርድ አባላት እና አመራሮች ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ታንዛንያ ገብተዋል።

የምክር ቤቱ ልዑክ በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ፍቃዱ በኢትዮጵያና ታንዛኒያ መካከል ስላለው ታሪካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና በሁለቱ አገራት መካከል ስላሉ የንግድ አማራጮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ አብዱልሃኪም ሙሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጉብኝቱ የኢትዮጵያን የውጭ ምርቶች ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስርን ለማጠናከርና ከታንዛንያ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ መዳረሻን ለማስፋት የሚያግዙ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም እንደሚያስችልም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከታንዛንያ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት የማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የወጭ ምርት እያደገ መምጣቱ ገልጸዋል።

ይህንንም የበለጠ ለማሳደግ ለግሉ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ጉብኝቱ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ልዑካን ቡድኑ በታንዛኒያ በሚኖረው የተለያዩ የታንዛኒያ ተቋማትን እንደሚጎበኝ እና የጋራ መግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረም በዳሬሰላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም