ቀጥታ፡

ፖሊሲው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን የሚያግዙ ጠንካራ የተቋማት ትብብር መፍጠር ያስችላል - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን የሚያግዙ ጠንካራ የተቋማት ትብብር መፍጠር የሚያስችል መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ የማጠቃለያ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ ወጥነት ያለውና የተቀናጀ የንግድ ሥርዓት አመራር አደረጃጀት መዘርጋት፣ ፍትሐዊ የንግድ ውድድር አውድ መፍጠር፣ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ሰፊና ተገማች የገበያ ዕድል ማፈላለግ፣ የግብይት መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ ማድረግን ያለመ ነው፡፡


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ ኢትዮጵያ የሚገመትና የሚተነበይ የንግድ ከባቢ እንዳላት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፖሊሲ የመንግሥት ምልከታና እይታ መሆኑን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ያላትን የንግድ እንቅስቃሴና ግልጸኝነት ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ ላይ የመንግሥትን አቋም ከማሳየት ባለፈ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የንግዱን ማህበረሰብ የሚያሳድግ መሆኑንም ተናገረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ የኢትዮጵያን የንግድ መልክዓ ምድር ያስረዳል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የዘርፉ ተዋንያን የሚመሩበትን አቅጣጫ እንደሚጠቁምም ገልጸዋል፡፡


 

ፖሊሲው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ንግዱን ከማነቃቃት ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ንግድ የሚኖራትን ተሳትፎ ያጎለብታል ብለዋል፡፡

ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ የሚያግዙ የተቋማት ትብብር መፍጠርና ማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት፡፡


 

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ በረከት ወርቁ በበኩላቸው፤ ፖሊሲው ለረጅም ጊዜ ስንጠብቀው የነበረ ነው ብለዋል፡፡

በወጭና ገቢ ንግድ አሰራር፣ በፋብሪካ ግብዓት አቅርቦት እና መሰል የንግድ እንቅስቃሴዎች በኩል የነበረውን ችግር የሚፈታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ፖሊሲው የሴቶችን ተሳትፎ በማጎልበትና ኮንትሮባንድን በማስቀረት የተሳለጠ የንግድ ከባቢ መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተናገረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም