የጋምቤላ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
ጋምቤላ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ከተማን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ(ዶ/ር) ገለፁ።
በከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎቱን ለማሻሻል ከ315 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት በከተሞች እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የውሃ መሰረተ ልማት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በተለይም አሁን ላይ በጋምቤላ ከተማ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር በተያይዘ እየታየ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በጊዜያዊነት ለመፍታት የማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦቱን ለማሻሸል እየተካሄዱ ከሚገኙት ስራዎች መካከል የ21 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ ተጨማሪ የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ተከላ፣ የማጠራቀሚያ ግንባታና ሌሎች የማሻሻያ ስራዎች ይገኙበታል ብለዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከሶስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ የከተማውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንደሚያሻሽል አብራርተዋል።
እንዲሁም የከተማውን ህዝብ ቁጥር መሰረት ያደረገ ጥናት በማካሄድና የሃብት ምንጭ በማፈላለግ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝም ሚኒስቴሩ አጋር አካላትን አስተባብሮ እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በተለይም በክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማይደስርባቸው አካባቢዎች የሚገነቡ የውሃ ተቋማትን የፀሃይ ኃይል አመራጮችን በመጠቀም አገልግሎቱን ዘላቂ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ኡዶል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማገዝ ረገድ ያልተቆጠበ ድጋፍ እያደረገ ነው።
በአሁኑ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) እና ሌሎች የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የውሃ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ላሳዩት ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ በሚኒስቴሩና በአጋር አካላት እየተከናወኑ የሚገኙ የውሃ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።