ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የፓኪስታንን የአቪዬሽን ዘርፍ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሔደ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እና በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሚስተር አቲፍ ሻኒፍ ኢትዮጵያና ፓኪስታን በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ ምክክር አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ያሳየችው ፍላጎት የሚደገፍ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊ ፈቃድ ወደ ፓኪስታን እያደረገ ያለውን በረራ አስፈላጊ ጉዳዮች ተሟልተው በቋሚነት ወደተለያዩ መዳረሻዎች ለመብረር እንዲችል የአየር አገልግሎት ስምምነት መፈራረም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪም በሌሎችም የአቪዬሽን ዘርፎች በጋራ መሥራት ከአቪዬሽን ባሻገር ለሁለቱም ሀገራት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም አብራርተዋል።

የፓኪስታን አምባሳደር በበኩላቸው ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ዘረፈ ብዙ ትብብሮችን ማድረግ እንደምትፈልግ ጠቁመው በአቪዬሽን ዘርፍ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ በሜዲካል ቱሪዝም፣በአቪዬሽን ሰው ኃይል ሥልጠናና በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት አንስተዋል።

አምባሳደሩ በገለፃቸው ፓኪስታን እንደ ህንድ፣ታይላንድና ማሌዥያ የሜዲካል ቱሪዝም ሰፊ አቅም እንዳላት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከካራቺና ኢስላምአባድ በተጨማሪ ወደ ላሆር እንዲበርና በሐጂና ኡምራ ጉዞ ወቅትም የበረራ አገልግሎት እንዲሰጥ ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።

በሂደት ላይ ያለው የአየር አገልግሎት ስምምነትን ተደራድሮ የመፈራረም የመረጃ ግንኙነት በማጠናቀቅ በቅርቡ ለመፈጸም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ፓኪስታን እያካሄደች ባለው የ”Single Country Exhibition” ኢኒሼቲቭ መሠረት ከ100 የማያንሱ የፓኪስታን ባለሀብቶች እ.ኤ.አ.ከሜይ 15-17∕2025 በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የወጪንግድ ኤግዝቪሽንና ባዛር እንደሚያካሂዱ መግለጻቸውን የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም