ኢትዮጵያ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ስርዓተ ምህዳርና የሎጂስቲክስ አቅም አላት - በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ስርዓተ ምህዳርና የሎጂስቲክስ አቅም አላት - በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ ስርዓተ ምህዳርና የሎጂስቲክስ አቅም አላት ሲሉ የተለያዩ በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ለግብርና ሥራ ተስማሚ የአየር ንብረት፣ ለም መሬትና ከፍተኛ የሰው ኃይል ያላት መሆኗ በዘርፉ መሰማራት አዋጭ መሆኑ ይገለጻል።
በኢትዮጵያ የደርባ አበባ እና ሙሎ ፋርም አስተባባሪ ራፋኤል ጆሊ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለግብርና ስራ ምቹና አስተማማኝ ስርዓተ ምህዳርን የታደለች ሀገር ነች።
በተጨማሪም ምርቶችንና ግብዓቶችን ከመነሻ ወደ መዳረሻ ለማጓጓዝ አስተማማኝ የሎጂስቲክስ አቅምና ከሌሎች ሀገራት ያነሰ የዕቃ ጭነት ክፍያ መኖሩንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ በመሆኑ የአትክልት፣ ፍራፍሬና የአበባ ልማት ዘርፉ አሁን ካለው የበለጠ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ተናግረዋል።
የደርባ አበባ እና ሙሎ ፋርም ኩባንያ በሀገሪቱ በግብርና ኢንቨስትመንት በመሰማራት ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያዎች በስፋት እያቀረበ ነው ብለዋል።
የአግሪ ፕላስት ኬንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኤርቱግሩል ሞሉሉ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጥራት ያላቸው የግብርና ምርቶችን በተለይም አበባን ማምረት የሚመች የአየር ሁኔታ እንዳላት ገልጸዋል።
በኢኮኖሚው መስክ እያደረገች ያለው ሪፎርም ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዳደረጋትም ጠቅሰዋል።
መንግሥት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች የሚያደርገው ድጋፍ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ወጪ ንግድን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ባለሃብቱ ያጋጥመው የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍታቱንም ነው ያነሱት።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈጻሚ ደረጀ አበበ እንደሚሉት፣ በለውጡ ዓመታት የግብርና ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ተሻሽለዋል ለባለሃብቱም ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በሰብል፣ በእንስሳት ልማት፣ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በውል እርሻ ልማት ኢንቨስትመንቶች በርካታ ባለሃብቶች መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም ከ6ሺህ በላይ ባለሃብቶች በሰብል ልማት ኢንቨስትመንት ተሰማርተው 2ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እያለሙ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከአርሶ አደሮችና ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መሬት በውል ወስደው በጋራ የሚያለሙበት ዕድል መፈጠሩንም አንስተዋል።
በዚህም በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ነው አቶ ደረጀ የገለጹት።
እንዲህ አይነቱ አሰራር የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከመፍጠር ባለፈ ባለሃብቱ የሚፈልገውን ምርት በጥራት እንዲያመርት እያደረገ ነው ብለዋል።