ቀጥታ፡

ለግብርና ሜካናይዜሽን የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ የምርትና ምርታማነት እድገት እያስገኘ ነው - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- ለግብርና ሜካናይዜሽን የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ የምርትና ምርታማነት እድገት እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ መንግስት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን በትኩረት አከናውኗል ብለዋል፡፡

የግብርና ሜካናይዜሽንን ከማስፋፋት አኳያ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅሰው፥ የእርሻ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ለአርሶ አደሮች ተደራሽ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡


 

በዚህም ባለፈው የመኸር ወቅት ከታረሰው 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 25 በመቶው በትራክተር መታረሱን ገልጸዋል።

የምርት ብክነትን በመከላከል ምርታማነትን ለማሳደግ በተሰጠው ትኩረት የደረሱ ሰብሎችን በኮምባይነር መሰብሰብ እየተለመደ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የሰብል ጤናን ለመጠበቅ የአንበጣ፣ የግሪሳ ወፍ እና የአረም መቆጣጠሪያ ኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖችን በመግዛት ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአዲስ ዕይታ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗንም ገልፀዋል።

ማዳበሪያን ጨምሮ ግብዓቶችን በራስ አቅም አምርቶ ማቅረብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነት ግብን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ እንደምትገነባ ማንሳታቸውን ያወሱት ሚኒስትሩ፥ ይህ ትልቅ ኢኒሼቲቭ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ግብዓትን በራስ አቅም በመሸፈን ለግብርናው ዘርፍ አዲስ የታሪክ እጥፋት እንደሚያመጣም ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ስርዓት እየገነባች እንደምትገኝም አክለዋል።

በዚህም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሁም በበጋ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ስራ እያከናወነች ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም