ቀጥታ፡

የሀይል አማራጮችን በማስፋት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው

ጅማ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- የሀይል አማራጮችን በማስፋት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጋምቤላ፤ ከፊል ኦሮሚያንና ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ለተውጣጡ የውሃና ኢነርጂ ባለሙያዎች በጅማ ከተማ በታዳሽ ሀይል ዙሪያ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናውም የሀይል አማራጮችን በማሰባጠር የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነት ማስፋፋትን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት የሀይል ምንጭ ስብጥርን በማስፋት የሀይል ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።


 

በተለይም መደበኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማያገኙ የገጠር አካባቢዎች በጸሀይ እና በንፋስ ሀይል ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት የሀይል ምንጭ እና አቅርቦት ስራዎች ላይ መንግስት ብቻ በስፋት ሲሰራ የቆየውን ተግባር በአሁኑ ሰአት የግሉ ዘርፍም እንዲሳተፍ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል 94 በመቶው ከውሃ ብቻ የሚገኝ እንደሆነ አንስተው ይህን ለመቀየር የሀይል አማራጮችን ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው ስልጠናው በየአካባቢያቸው የታዳሽ ሀይል አቅርቦትን ለማስፋፋትና ገጠር አካባቢዎች የሀይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር ያግዛል።

በጋምቤላ ክልል የኢነርጂ ቢሮ ባለሙያ አቶ ኡመድ ኦመድ ኦዲየል፤ ኤልክትሪክ የማያገኙ አካባቢዎች የጸሀይ ሀይልን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ ያዘጋጀው ስልጠናም በዘርፉ አቅማችንን ለማሳደግ እና የሀይል አማራጮችን መመልከት እንድንችል ያግዘናል ብለዋል።

የጅማ ዞን ውሀና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት የኢነርጂ ዘርፍ ቡድን መሪ አቶ ሸለማ በየራ፤ በጅማ ዞን በርካታ አካባቢዎች የመብራት አገልግሎት የማያገኙ በመሆናቸው ታዳሽ ሀይልን ተደራሽ ማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም