የኢትዮ-እስራኤል የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-እስራኤል የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 25/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ እና እስራኤል የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም የኢትዮ-እስራኤልን ንግድና ኢንቨስትመንት በማሳለጥ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያና እስራኤል ከጥንት መጽሐፍ ቅዱስና ንግስተ ሳባ ዘመናት የሚመነጭ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት ናቸው።
እ.አ.አ. ከ1948 የእስራኤል ምስረታ ማግስት የሀገራቱ ታሪካዊ ወዳጅነት በዘመናዊ ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት በመንግስት ለመንግስት፣ በግል ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የዲፕሎማሲ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
በመንግስት ለመንግስት ፖለቲካዊ የዲፕሎማሲ ትብብርን ለማጠናከር የሀገራቱ የስራ ኃላፊዎች ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግና የትብብር ስምምነት በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
በቅርቡም የእስራኤል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሀገራቱን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር መምከራቸውን አንስተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የተመራ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ልዑክም ወደ እስራኤል በማቅናት የጋራ ትብብርን የሚያጠናክር ስኬታማ ቆይታ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የሚካሄዱ የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትብብሮችን እያጠናከሩ ነው ብለዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት መስክም ከ122 ያላነሱ የእስራኤል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ እያደረጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ለአብነትም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የእርሻ፣ ውሃና ማዕድን ልማት፣ በግብርና ምርት ማቀነባበሪያና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እየተሳተፉ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በንግድም እስራኤል ከኢትዮጵያ ጤፍ፣ ቡና እና ሌሎች የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ከፍተኛ ተቀባይ ሀገር ናት ብለዋል።
ኢትዮጵያም የልማት አጋዥ የሆኑ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ከእስራኤል እንደምታስገባ ጠቅሰው፥ የሀገራቱ የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸው ከፍተኛ እድገት እያስዘመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስታዊ ያልሆኑ የእስራኤል ድርጅቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የትብብር ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
በግብርና፣ በትምህርትና በጤና ሰፋፊ የጋራ ስልጠና፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርትና ጤና ተቋማት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለኢትዮ-እስራኤል ሁለንተናዊ ትብብር በሁለቱ ሀገራት የሚኖሩ ቤተ-እስራኤላውያን ድልድይ ሆነው እያገለገሉ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በቀን ከሁለት ጊዜ በላይ ወደ እስራኤል የሚያደርገው በረራ የሀገራቱን የቱሪዝም፣ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማሳለጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እያጠናከረ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለገበያ ሥርዓት፣ ለባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገትና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት መሰጠቱ ለእስራኤል ባለሃብቶች ምቹ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሀገራቱን ታሪካዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ግንኙነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።