ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፉት ስምንት ወራት ከ20 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎቶች ሰጠ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 25/2017 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ባለፉት ስምንት ወራት ከ20 ሺህ በላይ የምርት ጥራት ፍተሻ አገልግሎቶች መስጠቱን አስታወቀ።

በተጨማሪም ከ25 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ላይ የላብራቶሪ ፍተሻ ተደርጓል፡፡

በተለያዩ ምርቶች ላይ የሚደረጉ የጥራት ፍተሻዎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ከመሆኑ በላይ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ ውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ያስችላሉ።

ድርጅቱ የጥራት ፍተሻና የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከሰጠ በኋላ በምርቶቹ ላይ በየሶስት ወሩ ፍተሻ ያደርጋል።

ፍተሻ ተደርጎባቸው ከሁለት ጊዜ በላይ የተቀመጠላቸውን የጥራት መስፈርት ያላሟሉ ምርቶችን ለሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል በምርቶቹ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግና እርምጃ እንዲወሰድ ያሳውቃል።

የድርጅቱ የማርኬቲንግ እና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተክኤ ብርሀነ ለኢዜአ እንዳሉት፥ድርጅቱ በዋናነት የጥራት ፍተሻ ላቦራቶሪ፣ የጥራት ሰርተፊኬሽን እና የኢንስፔክሽን አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል።

እነዚህ አገልግሎቶች የምርትና አገልግሎት ጥራትን ለመመዘንና ውጤት ለመስጠት የሚያስችሉ የጥራት መለኪያዎች ናቸው ብለዋል።

ድርጅቱ ባለፉት 8 ወራት ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ምርቶች በላብራቶሪ የጥራት ፍተሻና የሰርተፊኬሽን አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም 15 ሺህ 153 ፍተሻ፣4 ሺህ 067 ኢንስፔክሽን እንዲሁም 928 ሰርተፊኬሽን በጠቅላላው 20 ሺህ 148 አገልግሎቶች መሰጠቱን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ከ25 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ላይ የላብራቶሪ ፍተሻ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ምርቶቹ በተቀመጠላቸው መስፈርት መሰረት ደረጃቸውን ጠብቀው መመረታቸው ተፈትሾ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት የሚሰጣቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።

ድርጅቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተቀባይነት ያላቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የፍተሻ ላቦራቶሪዎቹ ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁና የህብረተሰቡን ደህንነትና ጤንነት ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።

ድርጅቱ የጥራት ፍተሻ አገልግሎት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል የግብርና ግብዓቶች፣ የምግብና መጠጥ፣ መድሃኒት፣ ኬሚካልና ማዕድን፣ የኮንስትራክሽን ግብዓት፣ የኤሌክትሮኒክስ የቆዳና ጨርቃጨርቅ ምርቶች ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት በክልል ከተሞች ዘጠኝ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን ህብረተሰቡ አስገዳጅ የጥራት ምልክቶችና የምርት ደረጃዎች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም