የብርሸለቆ መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሰረታዊ ወታደሮችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የብርሸለቆ መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መሰረታዊ ወታደሮችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 25/2017 (ኢዜአ)፦የብርሸለቆ መሠረታዊ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ 41ኛ ዙር መሰረታዊ ወታደሮችን አሥመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ በክብር እንግድነት በመገኘት ሰልጣኞችን የመረቁት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሃመድ ተሰማ ፣የመከላከያ ሃይልን በሰው ኃይል ልማት ከዘመኑ ወታደራዊና ቴክኖሎጂያዊ ትጥቆች በመደገፍ ውጤታማ ግዳጆችን እንዲወጣ ለማስቻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልፀዋል።
ውትድርና ሙያ ከሌሎች ሙያ ልዩ የሚያደርገው አንዱና ዋነኛው መንገድ ክብርና ውድ ህይወቱን ሰውቶ ሀገርን ማፅናት፣ ህዝብን ማገልገል የሚጠይቅ ሙያ ነው ብለዋል።
ሙያውን በጥብቅ ዲስፕሊን ለመፈጸም ደግሞ መሰልጠን ሙያው የሚጠይቀውን እውቀት ብቃት ችሎታ መፍጠርና በስነ-ልቦና መዘጋጀት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የ41ኛ ዙር ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች በውትድርና ሙያ አገራችሁንና ህዝባችሁን በፍፁም ታማኝነት ለማገልገል ፈቅዳችሁ፣ ሰልጥናችሁ ወደ ተቋሙ የተቀላቀላችሁ የጀግና ህዝብ ልጆች ስለሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በማሰልጠኛ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን መነሻ አቅም በመጠቀም በምትመደቡበት አሃድ ከነባሩ ሠራዊት የምታገኙትን ልምድና ተሞክሮ ጨምራችሁ በየጊዜው አቅማችሁንና ብቃታችሁን በማሳደግ የሚሰጣችሁን ህገ -መንግስታዊ ተልዕኮ ሠራዊቱ የተገነባባቸውን እሴቶችና ህዝባዊ ባህሪን ተላብሳችሁ በጀግንነት፣ በታዛዥነትና በፅኑ ዲስፕሊን ልትወጡ ይገባል ሲሉ አዛዡ ማሳሰባቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።