ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ስፖርት እድገት ድጋፍ ይደረጋል- ሞሪናሬ ዋታናቤ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 25/2017 (ኢዜአ)፡-ለኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ስፖርት እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሞሪናሬ ዋታናቤ ገለጹ።

የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታ አድርገዋል።

ዋታናቤ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አመራሮች፣ከኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።


 

ፕሬዚዳንቱ ለኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ስፖርት እድገት የፋይናንስ እና የጅምናስቲክ ስፖርት የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርጉና በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት ፕሬዚዳንቱ፥ ለስፖርቱ አድገት የዘርፉ ተዋንያን በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች እና ስልጠናዎች አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን አቶ ገበያው ታከለ በበኩላቸው፥ ፌዴሬሽኑ በቀጣይም መሰል ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ግንኙነቶችን ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሞሪናሬ ዋታናቤ በአዲስ አበባ የተገነቡ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸውን ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም