ኢትዮጵያውያን በሰውነታቸው ክብር እንዲያገኙ ማስቻል የሀገራዊ ለውጡ ዋነኛ መዳረሻ ግብ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን በሰውነታቸው ክብር እንዲያገኙ ማስቻል የሀገራዊ ለውጡ ዋነኛ መዳረሻ ግብ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያውያን በሰውነታቸው ክብር እንዲያገኙ ማስቻል የሀገራዊ ለውጡ ዋነኛ መዳረሻ ግብ ነው ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱ አመራርና ሠራተኞች የሀገራዊ ለውጡን 7ኛ ዓመት በማስመልከት "ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ባስተላለፉት መልዕክት ‹‹ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረው የለውጡ ሰባተኛ ዓመት ከትናንት የምንማርበት፣ ስለዛሬ አብዝተን የምንመክርበትና ለነገ መሰረት የምንጥለበት ነው ብለዋል፡፡
የለውጡ ጉዞ ትልልቅ ጉዳዮችን ከመሰረቱ መለወጥ የሚያስችሉ ተግባራት በተጨባጭ የተከናወነበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ያልተሞከረ ነገር ግን ለኢትዮጵያ ቀጣይነትና ዘላቂነት ግድ የሚሉ ጉዳዮች የተሞከሩበትና አዳዲስና ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡ እውን በሆነባቸው ዓመታት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራቶችን ማከምና ማዳን የሚያስችሉ ሰፋፊ ትልሞች የተቀረፁባቸው ከመሆኑም በላይ ቀን ከሌሊት በመትጋት ትውልድንና ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤቶች ዕውን የሆኑባቸው ጊዚያት እንደነበሩም አብራርተዋል፡፡
ከራስ በላይ ሀገር ማስቀደምና ፀንቶ መቆም የለውጡ ምሰሶዎች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ ኢትዮጵያውያን ከጋራ ማንነታቸው በላይ በሰውነታቸው ክብር እንዲያገኙ ማስቻል ደግሞ ዋነኛ መዳረሻ ግብ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት የተሠሩ ሥራዎች ኢትዮጵያን ለትውልድ የምትበቃ ሀገር እንድትሆን ማድረግ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታን የፈጠሩ መሆናቸውን በአፅንኦት አንስተዋል።
የማይቋረጠው የህዳሴ ጉዞ የኢትዮጵያ ልዕልና እስኪረጋገጥ ድረስ በፅናት ይቀጥላል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡