ቀጥታ፡

የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እንግዶች የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የወጣት ሚኒስትሮችና ወጣት አመራሮች ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል።

እንግዶቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝደንት ፉአድ ገና አቀባበል አድርገውላቸዋል።

እንግዶቹ የጅቡቲ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያ፣ የአልጄሪያ፣ የብሩንዲ እና የጋቦን ተወካዮች መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ "የወጣቶችን አቅም ለበለፀገች አፍሪካ" በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 25 እስከ 27 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በአድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

በጉባኤው ላይ ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት አመራሮችና የወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣት ምሁራን፣ ወጣት የማህበረሰብ አንቂዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም