የመጋቢት 24 ውጥኖችን በማፅናት ፍትሀዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን - ኢዜአ አማርኛ
የመጋቢት 24 ውጥኖችን በማፅናት ፍትሀዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦ የመጋቢት 24 ውጥኖችን በማፅናት ፍትሀዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።
የጤና ሚኒስቴር፣ የተጠሪ ተቋማትና የፌዴራል ሆስፒታሎች አመራሮችና ሰራተኞች “የመጋቢት 24 ውጥኖችን በማጽናት ፍትኃዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን!” በሚል መሪ መልዕክት የ7 ዓመታት የለውጥ ትሩፋቶችን በማስመልከት በጋራ አክብረዋል።
በመድረኩ የተገኙት ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በጤና ዘርፍ የመጋቢት 24 ውጥኖችን በማፅናት ፍትሀዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንተጋለን ሲሉ ገልጸዋል።
በለውጡ ሀገራችን እንደ ሀገር እንዲሁም በጤና ዘርፍ የተገኙ አንፀባራቂ ድሎችን ይበልጥ በማጠናከር ማስቀጠል እንዲሁም ያጋጠሙ ፈተናዎችን ወደ እድል በመቀየር የለውጡን ትሩፋቶች ማጽናት ያስፈልጋል ብለዋል።
ወንድማማችነት እና እህትማማችነትን መሰረት በማድረግ ሁሉም ባለቤት የሆነበት፣ የሚዲያ ነፃነት የተከበረበት እንዲሁም ከከፋፋይ ትርክት ወደ አንድነት ትርክት የተሸጋገረችበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ቀሪ ስራዎችን በጋራ ለመስራትም ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው የጤናው ዘርፍ የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ሁሉም አመራሮችና ሰራተኞች ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የህክምና ግብዓቶችን ከማምረት በተጨማሪ ከውጭ በሚመጣውና በሀገር ውስጥ በሚመረተው ግብዓት መካከል ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየር የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምድ መዳበር እንደሚገባውም አሳስበዋል።
በፕሮግራሙ ባለፉት 7 የለውጥ ዓመታት በጤናው ዘርፍ የመጡ ለውጦችን የሚያስቃኝ ዶክሜንታሪ ቀርቧል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታየ "የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች" በሚል ርዕስ ገለፃ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።