ዘመኑን በዋጀ አመራር ለውጡን ማጽናት ይገባል- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ - ኢዜአ አማርኛ
ዘመኑን በዋጀ አመራር ለውጡን ማጽናት ይገባል- ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 24/ 2017 (ኢዜአ)፦ ዘመኑን በዋጀ አመራር በለውጡ የተገኙ ውጤቶችን ማጽናት እንደሚገባ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች የለውጡን ሰባተኛ ዓመት በማስመልከት "ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና!" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሄደዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለውጡ ያልነካው ዘርፍ የለም ያሉ ሲሆን በባህል እና ስፖርት ዘርፍ የተደረጉ ሪፎርሞችን አንስተዋል።
የባህልና ስፖርት ዘርፍ ትልቅ ሀገራዊ ሚና እንዳለው ገልጸው ዘመኑን በዋጀ ለውጥና አሰራርን በሚገባ በመተግበር ለውጡን ይበልጥ ማጽናት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ "የመጋቢታዊያን የለውጥ ፍሬዎች እና የነገ ተስፋዎች !" በሚል ርዕስ የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የመጣው የለውጥ ሒደት ሕጋዊ ሥርዐትን ጠብቆ የመጣ እና ለለውጡ መምጣት የሕዝብ ፍላጎት ገፊ ኃይል እንደነበር ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ የመጡ ተግባራዊ ለውጦች የሚታዩና የሚለኩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
የወል ገዥ ትርክትን በሚገባ ማስረጽ እንደሚገባ ጠቅሰው በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ፣ ሥነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕሮፌሰር ) ጊዜው ከሰውና ዕድል ጋር ገጥሟል፤ ለሀገራችን ታሪክ ሠርተን የምንመሰገንበት መኾን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።
የጥበባት ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶት ለመድረክ ማድመቂያ ሳይሆን ለዓላማ ማስፈፀሚያ በመሆኑ ራሱን ችሎ መዋቅር እንደተዘረጋለት አመልክተዋል።
በለውጡ የተከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ለትውልድ የተሰጡ ገጸ በረከቶች ናቸው ብለዋል።
የመጣውን ለውጥ ማጽናት እና ማስቀጠል የሁላችንም ተግባር ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ማሳሰባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።