በሲዳማ ክልል በለውጡ ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ከ 60 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በለውጡ ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ከ 60 በመቶ በላይ ማድረስ ተችሏል
ሀዋሳ፤መጋቢት 24/2017 (ኢዜአ):- በሲዳማ ክልል በለውጡ ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ከ60 በመቶ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ ፡፡
በማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍም በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት አበረታች ስራዎች መሰራታቸው ተገልጿል፡፡
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በዘርፉ የተከናወኑትን ተግባራት አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የክልሉ የውሃ፤ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ጋኖሌ እንዳሉት፥ በክልሉ በለውጥ ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በ2012 ዓ.ም 38 ነጥብ 2 በመቶ ከነበረበት አሁን ላይ 60 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል ፡፡
ሽፋኑን ለማሳደግም 1 ሺህ 291 የውሃ ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውንና ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ 3 ሺህ 29 ተቋማት ተጠግነው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡
የውሃ ተቋማቱ ለህብረተሰቡ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ማህበረሰቡ በራሱ እንዲያስተዳድራቸውና ሲበላሹ እንዲያስጠግናችው መደረጉን አውስተዋል፡፡
በለውጡ መንግስት ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ መስኮች መካከል የማዕድን ዘርፍ ተጠቃሽ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ከበደ፥ በክልሉም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ቢሮው በጥናት የለያቸው ከ23 በላይ የተለያዩ ማዕድናት መኖራቸውን ገልፀው፥ይህንን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
በዚህም ከ23 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀብት እንዲያፈሩ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወንን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ባልሆነባቸው ሰባት የገጠር ከተሞች ላይ የፀሐይ ኃይል አማራጮች እየተተከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያለውን የመስኖ ልማት አቅም ለመጠቀምም ባለፉት ዓመታት ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ሊያለሙ የሚችሉ 78 የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራ ሰርቶ ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል ፡፡
ከነዚህ ውስጥም 29 ፕሮጀክቶች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መቻላቸውን የተናገሩት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ከ4 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት በዘመናዊ መስኖ ማልማት ያስቻሉ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡