ቀጥታ፡

የላቀ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017 (ኢዜአ)፦የላቀ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች “ትናንት፣ ዛሬና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ሀሳብ የመጋቢት 24 ሀገራዊ ለውጥን በፓናል ውይይት አክብረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፥ በሰባት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ሀገራዊ ለውጡ የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ መስኮች ዘርፈ ብዙ ስኬቶች መመዝገባቸውን አውስተዋል።

ያለፋት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ያንሰራራችበትና ተደማጭነትቷ ከፍ ያደረገችበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የዜጎችን ክብርና መብት እንዲጠበቅ ብሎም ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን በማድረግ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስጠበቀ መልኩ በትክክለኛ መንገድ እየተጓዘ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በቀጣይ የዜጎች ክብርና ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል በማድረግ የላቀ የዲፕሎማሲ ስኬቶችን ለማስመዝገብ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በመድረኩ ላይ ከትርክት አኳያ፣ከቱሪዝም፣ከዲጂታል ኢኮኖሚ፣ከውጭ ጉዳይ አኳያ ትናንት፣ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና ላይ ያተኮሩ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም