ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ሊጀመር ነው

ባህር ዳር፤መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የሚጀመር መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትብብር የተዘጋጀው በአማራ ክልል ለሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የቅድመ ውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት በ10 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በስኬት ማከናወኑን አንስተዋል።

የምክክር ሂደቱ በሁሉም አካባቢዎች በጥሩ ሁኔታ መቀጠሉን ጠቅሰው፥ በቀጣይ ቀናት በአማራ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ቀደም ሲል በ259 ወረዳዎች የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ መከናወኑን አስታውሰው፥ ከመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ የሚጀመር መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

በክልሉ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በአካታችና አሳታፊነት የሚካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሀገራዊ ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፥ በሂደቱ ሁሉም በንቃት እንዲሳተፍ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

በትግራይ ክልልም በተመሳሳይ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተው፥ የትኛውም ችግር በምክክርና በሀሳብ የበላይነት እንዲፈታ ኮሚሽኑ አስቻይ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጰያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ የጋራ ሀገራዊ ችግሮችን በሰለጠነ አግባብ ለመፍታት የምክክር ሂደቱ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ምሁራን፣የሲቪክ ማህበራት እና አጠቃላይ ህዝቡ ለምክክር ሂደቱ መሳካት ትብብርና ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣አርቲስቶች፣የፖለቲካ ፖርቲ ተወካዮች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም