በመዲናዋ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቦችን ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡና የከተማዋንም ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ሀገራዊ ለውጥ እውን የሆነበት 7ኛ ዓመት አስመልክቶ "ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና" በሚል መሪ ሃሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት፥ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ ብሎም በመዲናዋ አያሌ ስኬቶች ተመዝግበዋል።
ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሠረት የጣሉ አመርቂ ስራዎች መከናወናቸውን ያነሱት ምክትል ከንቲባው፥ የኢትዮጵያ ቀጣይ መዳረሻ ብሩህ መሆኑን ያመላከቱ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በፖለቲካ፣ኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣በዲፕሎማሲው፣በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሰው ተኮር ስራዎች የሀገርን የቀጣይ ትልም ያመላከቱ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የተከናወኑ የልማት ስራዎችም የከተማዋን የብልጽግና ተምሣሌትነት በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፥ ሀገራዊ ለውጡ በህዝቡ ተቀባይነት ያገኘ፣ ብሎም የመደመር እሳቤን ለሀገር ያበረከተ ነው ብለዋል።
ለውጡ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ያደረገ መሆኑን ተናግረው፥ በፈተናዎች ውስጥ ዕድልን በማውጣት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ትልልቅ ሃሰቦች ታቅደው እውን የሆኑበት እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡