ቀጥታ፡

የለውጡ አመታት ኢትዮጵያን ከውስብስብ ችግሮች የታደገና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለበት ያመቻቸ ነው

ደሴ፤መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡-የለውጡ አመታት ኢትዮጵያን ከውስብስብ ችግሮች የታደገና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለበት ያመቻቸ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ።

የመጋቢት 24 ትሩፋቶችን ምክንያት በማድረግ የብልፅግና ፓርቲ አደረጃጀት፣የአመራርና አባላት የስነ ምግባር መመሪያና ደንቦች ዙሪያ ለአመራሩና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና በደሴ ከተማ ተሰጥቷል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንደገለጹት፤መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና የተበሰረበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡

ዕለቱ ኢትዮጵያን ከውስብስብ ችግሮች የታደገና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለበት ያመቻቸ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ በሂደትም በልማትና መልካም አስተዳደር ዘርፎች አበረታች ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በደሴ ከተማም የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች መልስ የተሰጠበት ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የኮሪደር ልማት፣ ሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ ዘመናዊ መናኸሪያ፣ የሥራ እድል መፍጠሪያ ሼዶችና የህዝብ መድሃኒት ቤቶችም መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የተጀመሩ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

አመራሩ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመጋቢት 24 የተገኙ ድሎችንና ፍሬዎችን ማስቀጠል እንዲችል በየደረጃው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ለውጤታማነቱም ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ በበኩላቸው፥ ፓርቲው መነሻና መድረሻ ዕቅድ ይዞ የሚፈፅም፣ ግልጽና ሰው ተኮር ልማቶችን በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ጭምር በማሳተፍ ባለፉት ሰባት ዓመታት የተከናወኑ የሰላም ግንባታ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል፡፡

በተለይ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ፣በገበታ ለሀገርና ለትውልድ፣በሌማት ትሩፋትና በስንዴ ልማት ላይ የተገኙትን ውጤቶችንም አመላክተዋል።

ሰልጣኞቹ በሰጡት አስተያየት፤ ስልጠና ባለፉት ዓመታት የተገኙ ድሎችን በማስቀጠል የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም