ቀጥታ፡

መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነው - ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦ መጋቢት 24 ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በዲፕሎማሲያዊ መስኮች በታሪኳ ያልተሞከረውን አዲስ መንገድ የጀመረችበት ቀን ነውሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ዕለቱ ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍና ቅኝት፣ በመሃል የፖለቲካ እይታ እየተመራች ካለፈው በጎውን በመውሰድ፣ ለነገው ትውልድ ዛሬ ላይ አዲስ አሻራ በማኖር የከፍታ ምዕራፍ የጀመረችበት ነው ሲሉ አስፍረዋል።

በውስብስብ ብዝሃነትና በርካታ ማንነት የመበታተን አደጋን በማለፍ ብዝሃነትን እንደ ጌጥ ተጠቅማ ህብረ ብሔራዊ አንድነቷን ይበልጥ ማጠናከር የጀመረችበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በለውጡ ዓመታት በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ በከተማና መሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ኢትዮጵያ የተቃጣባትን ሁሉንም ችግሮች መክታ ልዕልናዋን በማረጋገጥ ፈጣን ለውጥና እድገት ማስመዝገቧንም ገልጸዋል፡፡

ዜጎች የሰላም አየር እንዲተነፍሱ ዘመናዊ፣ የሰለጠነና በሐሳብ የበላይነት የሚመራ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣት መጀመሩንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

የተመዘገቡ ድሎችን ቆጥሮ ዘላቂነታቸውን መጠበቅና ማስፋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የዜጎችን ህይወት ለመለወጥ፣ ሀገራዊ ህልምና ራዕይን ለማሳካት ድሎቻችንን እያስቀጠልን፣ ጉድለቶቻችንን እያረምን በላቀ ትጋትና ቁርጠኝነት ልንረባረብ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም