ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ለተጀመረው የምክክር ሂደት ሁሉም የመፍትሄው አካል ሊሆን ይገባል - ፕሮፌሰር መስፋን አርዓያ

ባህርዳር፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ለተጀመረው የምክክር ሂደት ሁሉም የመፍትሄው አካል ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፋን አርዓያ ተናገሩ።

በአማራ ክልል የምክክር ሂደት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ የውይይት መድረክ በባህርዳር ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ምእራፎችን በማለፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምእራፍ ላይ መድረሱን ተናግረው በዚህ ሂደትም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማሳተፉን አንስተዋል።

በሂደቱ አካታችና ሁሉንም አሳታፊ ያደረገ የምክክር ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናከረና ውጤት በሚያመጣ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ የጋራ መፍትሄ ለመሻት ኢትዮጵያ እየመከረች ትገኛለች ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ በዚህ አካታችና አሳታፊ የምክክር ሂደት በአማራ ክልልም የነቃ ተሳትፎና እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ ለመጡ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄው ምክክር መሆኑን አንስተው የዚሁ መፍትሄ አካል ለመሆን ሁሉም ሊዘጋጅ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ የፖለቲካ ፖርቲ ተወካዮች፣ የህግ ባለሙያዎች እና ሌሎችም አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ኘሬስ ድርጅት ትብብር መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም