የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የጅምናስቲክ ስፖርት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የጅምናስቲክ ስፖርት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- የዓለም አቀፉ የጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ የጅምናስቲክስ ስፖርት እድገት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ሞሪናሬ ዋታናቤን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው መንግስት ለስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት የጅምናስቲክስ ስፖርት መሠረተ ልማቶችን በሚገነቡ በሁሉም መሠረተ ልማቶች ላይ ተካቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ በአዲስ አበባ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን፣ በአዲስ አበባ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም እና በአዲስ ኮንቬንሽን ሴንተር የጅምናስቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውንም አመልክተዋል።
የዓለም አቀፉ ጅምናስቲክስ ፌዴሬሽን ሞሪናሬ ዋታናቤ ፌዴሬሽኑ ለኢትዮጵያ የቴክኒክ፣ የስፖርት ቁሳቁስ እና የስልጠና ድጋፎችን እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ በቆይታቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የጅምናስቲክስ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ሴንተርን እንደሚጎበኙ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።