ቀጥታ፡

የአሜሪካ አውሮራ ከተማ ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት አላት - የከተማዋ ከንቲባ ማይክል ኮፍማን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፡- የአሜሪካ አውሮራ ከተማ የባህል ልውውጥ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት የከተማዋ ከንቲባ ማይክል ኮፍማን ገለጹ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም በኮሎራዶ ግዛት በምትገኘው አውሮራ ከተማ ከንቲባ ማይክል ኮፍማን የተመራ ልዑክን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አምባሳደሩ በኮሎራዶ በምትገኘው አውሮራ ከተማ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ውይይቱ በቀጣይ ለሚኖሩ የከተማ ለከተማ ጉድኝቶች፣ ለንግድና ኢንቨስትመንት ትብብሮች አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

በርካታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በከተማዋ መኖራቸው በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ ላለው የባህል ልውውጥ ማጎልበት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ለዚህም ስኬት ኤምባሲው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የአውሮራ ከተማ ከንቲባ ማይክል ኮፍማን አውሮራ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት ከተማና ከተለያዩ ማህበረሰቦች አንጻር በቁጥሩ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ ማህበረሰብ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተማዋ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለከተማዋ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እሴት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አመልክተዋል።

በከተማዋ ከ118 የሚበልጡ በኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚመሩ የንግድ ተቋማት እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በቅርቡ የከተማዋ ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አምሳሉ ካሳው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በከተማዋ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።

የልዑክ ቡድኑ አባላት በከተማና ተቋማት ጉድኝቶች፣ በኢንቨስትመንት እና በባህል ልውውጦች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም