ቀጥታ፡

የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2017(ኢዜአ)፦ የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመጋቢት 24 ትሩፋቶች እና ሀገራዊ ለውጡን በተመለከተ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል

በመልዕክታቸውም መጋቢት 24 በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት ብለዋል፡፡

ትናንትን እና ዛሬን፤ ዛሬን እና ነገን፤ የዳርና የመሐልን፤ ግንባር እና አጋርን፤ አርሶ እና አርብቶ አደርን፣ ግለሰብና ቡድንን፣ አካቢያዊ እና ሀገራዊ ማንነትን፣ በመደመር ዕሳቤ ያግባባች ቀን ናት ሲሉም ገልጸዋል፡፡ 

ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመጓዝ መነሻ ሆናለች፡፡ ለመፍጠርና ለመፍጠን የሚያስችል ዐውድ ዘርግታለች፡፡ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት ሀገር የሚቀይሩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዲጨረሱ፤ ተጠናቅቀው እንዲመረቁ አስችላለች፡፡ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሐሳቦች ከዕንቅፋት ተርፈው ለብርሃን እንዲበቁ አድርጋለች ብለዋል፡፡ 

በይቅርታ እንሻገር፣ በፍቅር እንደመር፤ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ፤ አረንጓዴ ዐሻራ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ፤ የሌማት ትሩፋት፣ የምግብ ሉዓላዊነት፤ የትምህርት ቤት ምገባ፤ የኮሪደር ልማት፤ ወዘተ ተነሣሽነቶች የመጋቢት 24 ውጤቶች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሪፎርም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፤ የውጭ ግንኙነት ሪፎርም፤ የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም፤ የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም፤ የሚዲያ ሪፎርም፤ ወዘተ… የመጋቢት 24 ፍሬዎች ናቸው ብለዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት እየራቀ፣ ነገ እየቀረበ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተገቢዋን ቦታ ለመያዝ ተቃርባለች ነው ያሉት፡፡

በመደመር ጎዳና፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የተጀመሩት ሥራዎች ሁሉ ፍሬያቸውን ማሳየት ጀምረዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድህነትና ኋላቀርነት ይነሳ የነበረው ስሟ በስንዴ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የቱሪስት መዳረሻ ምቹ ቦታዎች፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ወዘተ… በጎ ገፅታዎች መጠራት ጀምሯል ብለዋል። 

ዘርፈ ብዙ የመጋቢት 24 የለውጥ ፍሬዎችን መከባከብና ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ፍሬዎችን ከጃርቶች እና ከቀበሮዎች መጠበቅም አለብን ነው ያሉት፡፡

ማንም ከመዳረሻችን አያስቀረንም፡፡ ማንም እንዲያዘገየንም አንፈቅድም፡፡ በሚወረወሩብን ድንጋዮች ብልጽግናን እንገነባበታለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በየአንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን ብለዋል፡፡
                           

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም