ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት(ጋቪ) የክትባት ተደራሽነትና የጤና ስርዓት ማጠናከርን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር በቅርበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ከዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት(ጋቪ) አመራሮች ጋር በጥምረቱ መቀመጫ ጄኔቫ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ፀጋአብ ውይይቱን ያደረጉት ከጋቪ የዓለም ለጋሾች ግንኙነት ዳይሬክተር ቢዮርን ጊልሳተር እና በክትባት ከፍተኛ ለውጥ ያመጡ ሀገራት ቡድን ዳይሬክተር ቶክንቦ ኦሺን ጋር ነው።
ውይይቱ ጋቪ እ.አ.አ ከ2026 እስከ 2030 ለሚተገብረው አዲስ ስትራቴጂ ድጋፍ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
ስትራቴጂው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በክትባት 500 ሚሊዮን ህጻናትን ለመጠበቅ እና ስምንት ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናትን ደግሞ ከሞት ለመታደግ እቅድ ይዟል።
አምባሳደር ፀጋአብ ኢትዮጵያ ከጋቪ ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት እንዳላትና ስትራቴጂው የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ቋሚ መልዕክተኛው ኢትዮጵያ በክትባት የሰዎች በሽታ የመከላከል አቅም ለማሳደግ ለሚከናወኑ ስራዎች ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ በጽኑ ታምናለች ብለዋል።
በሀገር ውስጥ አቅም ክትባት የማምረት እና የጤና ስርዓት አይበገሬነትን ማጠናከር ትኩረት እንደሚያሻውም ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት(ጋቪ) አመራሮች ኢትዮጵያ ለሁሉም ህጻናት ክትባት ተደራሽ የማድረግ ዓለም አቀፍ ግብ(zero-dose children) ትግበራ ያሳየችውን ለውጥ እና ከጥምረቱ ጋር በጋራ በመሆን ከፍተኛ ውጤቶችን እያስገኙ ያሉ ኢኒሼቲቮችን በመተግበር እያሳየች ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ከጋቪ ጋር ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የዓለም የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥል ኢዜአ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
እ.አ.አ በ2000 የተቋቋመው ከዓለም አቀፉ የክትባት ጥምረት(ጋቪ) በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት የክትባት ተደራሽነትን በማሳደግ ዜጎች የበሽታ መከላከልን አቅም ማጠናንከር ላይ የሚሰራ ድርጅት ነው።