ቀጥታ፡

አምባሳደር እስክንድር ይርጋ ከጀርመን የቡና ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር እስክንድር ይርጋ ከጀርመን የቡና ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆልገር ፕሬቢሽ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በጀርመን እና በአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን የቡና ኤክስፖርት መጠን ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

በተጨማሪም ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያ አምራቾች እና ላኪዎች ከአውሮፓ ህብረት የደን ጭፍጨፋ ቁጥጥር ደንብን ተከትለው ምርት ማቅረብ በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይም መክረዋል።

ጀርመን የኢትዮጵያ የቡና መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትቀመጥ በበርሊን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ በ1886 የተቋቋመው የጀርመን ቡና ማህበር የሀገሪቱን የቡና ኢንዱስትሪ የሚወክል ግዙፍ የንግድ ማህበር ነው።

ማህበሩ በቡና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ 380 ኩባንያዎችን ይወክላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም