ማኅበሩ ለወል ትርክት ግንባታ ስኬት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል- ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ - ኢዜአ አማርኛ
ማኅበሩ ለወል ትርክት ግንባታ ስኬት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል- ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር በሀገር ግንባታ እና በወል ትርክት ግንባታ ስኬት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ጠየቁ።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር አመራር እና አባላት ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ሚኒስቴሩ እና ማህበሩ በትብብር መስራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ የታሪክ ምሁራን ማህበሩ እያበረከተ ላለው አስተዋፅኦ ዕውቅና ሰጥተዋል።
ማህበሩ ሀገርን በመገንባት ሂደት ያለበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበው በተለይ ለወል ትርክት ግንባታ ስኬት የበኩሉን ለመወጣት የገባውን ቃል ኪዳን እንዲያከብር ጠይቀዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታ እና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው መንግስት የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማሳካት መንግስት በህብረተሰቡ ዘንድ የወል ትርክትን ማስረፅ ቁልፍ ተግባር መሆኑን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድም ከማህበሩ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የታሪክ ምሁራን ማህበር ፕሬዝዳንት ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ማህበሩ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ታሪክን ማስረጽ ላይ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይ ማህበሩ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማጠናከር ላይ በጥናት የተደገፈ ስራ ለመስራት ከመግባባት ላይ መድረሱን የሰላም ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ሁለቱም ተቋማት በጋራ በሚሰሯቸው ስራዎች ዙሪያ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ተስማምተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት የወል ትርክት ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና መሰረት በማድረግ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።