ቀጥታ፡

ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ማጠናከር ትሻለች- አምባሳደር ጆሹዋ ታባህ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ካናዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጁዋ ታባህ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሹዋ ታባህ ከኢዜአ በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ እና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1965 መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

የሀገራቱ ግንኙነት በዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም የባለብዝሃ ወገን ትብብር እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።

በካናዳ ከ50 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚኖሩ ጠቁመው ይህም የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንዲጎለብት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ እና ቶርንቶ መካከል ያለው ዕለታዊ በረራ የሀገራቱን ትስስር እንዲሳለጥ አድርጓል ነው ያሉት አምባሳደሩ።

ከኢኮኖሚ ትብብር ረገድ ካናዳ ለኢትዮጵያ የምታደርገው የልማት ድጋፍ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በዋናነት በስርዓተ ፆታ እኩልነት፣ የግብርና ምርታማነት እና ሰብዓዊ እርዳታ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

የካናዳ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን ገልጸው፤ ሁለቱ ሀገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ትብብርም እያደገ መምጣቱን ነው ያነሱት።

ቡና፣ የእጅ ስራ ውጤቶች እና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በካናዳ ገበያ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ከመጣ የኢትዮጵያ ምርቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ካናዳ የቀድሞ ተዋጊዎች ትጥቅ የማስፈታትና የተሃድሶ ሂደት (ዲዲአር) ሂደት እየደገፈች እንደምትገኝ ገልጸው ሂደቱ ለመረጋጋት እና ለማህበራዊ መስተጋብር መጠናከር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

በዚህም ካናዳ ከኢትዮጵያ እና አፍሪካ ጠንካራ እና ከጊዜው ጋር የሚሄድ አጋርነት በመፍጠር ለአህጉሪቷ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ልማት፣ ንግድ እና ዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት አበክራ እንደምትሰራ አምባሳደሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም