ኢትዮጵያ በምክር ቤት አባልነት ቆይታዋ ለአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አበክራ ትሰራለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምክር ቤት አባልነት ቆይታዋ ለአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አበክራ ትሰራለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ቆይታዋ ለአህጉሪቷ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት አበክራ እንደምትሰራ በሕብረቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ገለፁ።
ኢትዮጵያ ለሶስት ዓመት እንድታገለግል በተመረጠችበት የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት ስራዋን ዛሬ በይፋ ጀምራለች።
የምክር ቤቱ አዲስ አባላት የአቀባበል ስነ ስርዓት ዛሬ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ተካሄዷል።
በስነ ስርዓቱ ላይ በአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ኢትዮጵያ በቆይታዋ ለአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት አበክራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
46ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባደረገው መደበኛ ስብስባ ኢትዮጵያ እና ኢስዋቲንን አዲሱ የህብረቱ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል አድርጎ መምረጡ የሚታወስ ነው።
ናይጄሪያ እና ካሜሮን የምክር ቤቱ አባል ሆነው በድጋሚ መመረጣቸው አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባላት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በግጭት አፈታት፣ ሰላምን ማስፈን እና በሰላም ግንባታ ያላትን የረጅም ጊዜ ልምድ እና አቅም በመጠቀም በአፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጿል።
.
በአቀባባል ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ለአዲስ እና በድጋሚ ለተመረጡ አባላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።
አምባሳደር ባንኮሌ ምክር ቤቱ የአፍሪካ የግጭት መከላከል፣ አፈታት እና አስተዳደር ጠንካራ ማዕቀፍ ሆኖ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የፈረንጆች አፕሪል ወር ሊቀመንበር አምባሳደር ሬቤካ አሙጌ ኦቴንጎ በበኩላቸው አዲስ ተመራጭ የምክር ቤቱ አባላት የአህጉሪቷን ሰላም እና መረጋጋት የማረጋገጥ አቅም እና ልምድ እንዳላቸው ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።