ሁሉን ያሳተፈ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት ጠንካራ ሀገርና ዴሞክራሲ ለመገንባት አጋዥ ነው - የጋራ ምክር ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉን ያሳተፈ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት ጠንካራ ሀገርና ዴሞክራሲ ለመገንባት አጋዥ ነው - የጋራ ምክር ቤቱ
ሚዛን አማን፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ የፖለቲካ ሥርዓት መዘርጋት ጠንካራ ሀገርና ዴሞክራሲ ለመገንባት አጋዥ መሆኑን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ክንፍ መደበኛ ጉባኤ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አየለ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት ከለውጡ በኋላ ለሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በዚህም ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን መፍጠር እንደተቻለ ጠቅሰው በትብብርና መስተካከል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ትግል በማድረግ በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ክንፍ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህም ጠንካራ ሀገርን ለመገንባትና የዴሞክራሲ ልምምድን ከፍ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም አደረጃጀቱን ለማጠናከር አየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሴቶችን ወክለው በመድረኩ የተገኙት ወይዘሮ ዚነት ዳዊት በበኩላቸው በክልሉ ያለውን የፖለቲካ እና የልማት እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁላችንም ድርሻ ነው ብለዋል።
ከካፋ አረንጓዴ ፓርቲ የተወከለው ወጣት ጤንነት ወርቁ በበኩሉ በክልሉ ያለውን ሰፊ የእርሻ መሬት በማልማት ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብሏል።
ሚዛን አማን ከተማ በተካሄደው የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶቸ፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ክንፍ መደበኛ ጉባኤ የሦስቱም ክንፎች የሥራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ተካሂዷል።