ድህነትን መሻገርና ለትውልዱ መልካም ስነ-ምግባር ማስተላለፍ የሚቻለው ልዩነትን ወደ ጎን በመተው አብሮነትን በማጠናከር ብቻ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ድህነትን መሻገርና ለትውልዱ መልካም ስነ-ምግባር ማስተላለፍ የሚቻለው ልዩነትን ወደ ጎን በመተው አብሮነትን በማጠናከር ብቻ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ድህነትን መሻገርና ለትውልዱ መልካም ስነ-ምግባር ማስተላለፍ የሚቻለው ልዩነትን ወደ ጎን በመተው አብሮነትን በማጠናከር ብቻ መሆኑን የተለያዩ ሃይማኖት መምህራን ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን ሃይማኖት ሳይለያቸው ለዘመናት የሰላም፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴትን በመላበስ በሚኖሩበት ቦታ በደስታና በሃዘን አንድ ላይ በመቆም ይታወቃሉ፡፡
ለዚህም የእምነት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይህንኑ እሴት የእለት ተእለት የኑሮ መርህ በማድረግ ለትውልዱ መልካም ምግባርን ማስተላለፍ እንደሚገባ የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ መምህራን ለኢዜአ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ የጥናትና ምርምር መምሪያ ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንድነትና አብሮነት ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው አንስተዋል።
አንድነትን ከሚሰብኩ አስተምህሮዎች መካከል ፈጣሪ የሰውን ልጅ ከአንድ ዘር መፍጠሩንና ሁሉም ሰው የሰው ዘር ነው የሚለው አስተምህሮ የሰው ልጆች አንድ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ይላሉ።
የአዳምና ሔዋን መፈጠር የሰው ልጆች አንዱ ለአንዱ አጋር፣ አጋዠና ተባባሪ የመሆን መገለጫ ነው ብለዋል።
በመሆኑም አብሮነትን የሚያጠናክሩና አንድነትን የሚሰብኩ አስተምህሮዎችን ወደ ተግባር በመቀየር ለጋራ ትርክት ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የእቅድ ጥናትና ፖሊሲ አገልግሎት ኃላፊ ሃጂ ኑረዲን ጀማል በበኩላቸው በእስልምና ሃይማኖት አብሮነትን የሚገልጹና መከባበርን የሚያጎሉ አስተምህሮዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።
በቅዱስ ቁርአን የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን የሚገልጹ አስተምህሮዎች በስፋት እንዳሉ ጠቁመው የሰው ልጅ ተደጋግፎና ተዛዝኖ መኖር እንዳለበትም በግልጽ መቀመጡን ነው የገለጹት።
የአብሮነት አስተምህሮ ለስነ-ምግባር መጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል ሃጂ ኑረዲን ጀማል።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ዮሃንስ ግርማ ሰዎች የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የፍላጎት ልዩነት ቢኖራቸውም የጋራ የሚያደርጓቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ ብለዋል።
በተለይም በወንጌላውያን አስተምህሮ ፈጣሪ ለፍቅር ሲል የከፈለውን ዋጋ ለማቆየት ሰዎች ከመከፋፈል፣ ከጸብና ጥላቻ ተቆጥበው እንዲኖሩ እንደሚያዝም ተናግረዋል፡፡
ድህነትን መሻገርና ለትውልዱ መልካም ስነ-ምግባር ማስተላለፍ የሚቻለው ልዩነትን ወደ ጎን በመተው አንድነትን በማጠናከር ብቻ መሆኑንም አመልክተዋል።