ኢትዮጵያ ከማምረት በሚነሳ የንግድ ስትራቴጂ የወጪ ንግድ መዳረሻዋን ማሳደግ ችላለች - ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከማምረት የሚነሳ የንግድ ስትራቴጂ በመከተል የወጪ ንግድ መዳረሻዋንና ተወዳዳሪነቷን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናን ከተወሰኑ ሀገራት ጋር በሙከራ ደረጃ በቅርቡ በመጀመር ለአፍሪካውያን የእርስ በርስ ንግድ መጠናከር የመሪነት ሚናዋን ትወጣለች ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ብዝሃነትና ተወዳዳሪነት ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በ2010 በጀት ዓመት ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር አስታውሰው፤ በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት ብቻ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በወጪ ንግድ ምርትና ምርታማነት ላይ የተከናወኑ ተግባራት፣ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራና የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲወሰን መደረጉ እመርታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ልክ ይህ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ የንግድ ዘርፉ በቢሮክራሲ ተተብትቦና ተዘግቶ ከቆየበት ዘመን አንፃር ተስፋ ሰጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በለውጡ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከቡና ምርት የወጪ ንግድ የሚገኘው ዓመታዊ ገቢ 700 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ ዘንድሮ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ የቡና ተክል በማልማትና በጥራት በማምረት በኩል የተከናወኑ ተግባራት ለተወዳዳሪነቱ የጎላ አበርክቶ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከማምረት የሚነሳ የንግድ ስትራቴጂ በመከተሏ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነቷ እያደገ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡

ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች የመዳረሻ ችግር ነበረባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኮንትሮባንድን በመከላከልና የመዳረሻ ገበያዎችን በማስፋት ከዓለም ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሀገራዊ ጥቅል ምርት አንጻር የወጪ ንግድ ገቢዋ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና እና የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ጥያቄ መዳረሻቸው ንግዱን ማስፋት መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓትን በመከተል የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ገበያ ተገማችና ተወዳዳሪ ለማድረግ ከዚህም በላይ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣናን በሙከራ ደረጃ መጀመር የሚያስችላትን ዝግጅት ማጠናቀቋን ገልጸዋል፡፡

አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናው ለኢትዮጵያ ተስፋ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በስፋት እየተመረቱ የሚገኙ የቡና፣ ጥራጥሬ እና ሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶችን በመላክ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም