ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያላትን እምቅ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ መንግስት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ምህዳር ፈጥሯል - ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያላትን እምቅ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ መንግስት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ምህዳር መፍጠሩን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለፁ።

ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ስምንት ወራት ከዘርፉ 366 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰው፥ በርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጥራቸውን አንስተዋል።

መንግስት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፥ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ እና የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ስትራቴጂን ጨምሮ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ከባቢ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያውም ለአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ትልቅ ዕድል አምጥቷል ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና ላኪዎች ማህበር የቦርድ ሊቀ-መንበር ነጋ መኳንንት፥ ኢትዮጵያ በአበባ ምርት ያላትን አቅም በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን መቻሏን ገልፀዋል።

መንግስት የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ በዘርፉ ለተሰማሩ አልሚዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አበባ አትክልተና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ቴድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፥ ለሶስት ቀናት በሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ 153 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ አንስተዋል።

ዓለም አቀፍ አቅራቢዎች ከኢትዮጵያ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ነውም ብለዋል፡፡

በኤክስፖው የተሳተፉት የሉና ኤክስፖርት ማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ማናጀር ሃይማኖት በኩረ ኤክስፖው ከተለያዩ አምራቾች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮ-ሃይላንድና ላፍቶ አበባ እርሻ ስራ አስኪያጅ እመቤት ተስፋዬ በበኩላቸው፥ ኤክስፖው የቴክኖሎጂና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኤክስፖው በማዳበሪያ አቅርቦት፣ በኬሚካል፣ በግሪን ሀውስ፣ በግብርና እቃዎች እንዲሁም በአግሮ ሎጂስቲክስ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እና አማካሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም