ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣው ማሻሻያ አዋጅ ክፈተቶችን በማስተካከል ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣው ማሻሻያ አዋጅ ቀደም ሲል የተፈጠሩ የአተገባበር ክፍተቶችን ለመሙላትና የአዋጁን አፈጻጸም ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 22ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን ማሻሻያ አዋጅ በሁለት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ስለማሻሻያ አዋጁ አጭር መግለጫ እና ሞሽን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በዚህም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት የስልጣን ክፍፍል እንደተጠበቀ ሆኖ የፌዴራሉ መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበት ልዩ ሁኔታ በህገ መንግስቱ በግልጽ ተደንግጎ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በዚህም ማንኛውም ክልል ህገ መንግስቱን በመጣስ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ከሆነ፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚሰጥ ትዕዛዝ መሰረት የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ ሊገባ እንደሚችል መደንገጉን ጠቁመዋል።

እነዚህን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች መነሻ በማድረግ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ስለሚመራበት ስርዓት አዋጅ ወጥቶ ተግባራዊ መደረጉን አውስተዋል።

አዋጁ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ትዕዛዝ መሰረት የፌዴራል መንግስት የክልል ምክር ቤትና የህግ አስፈጻሚውን በማገድ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ሊወስን የሚችልበትን ስርዓት ማስቀመጡን አመላክተዋል።

የማሻሻያ አዋጁ በቀደመው አዋጅ በአተገባበር ወቅት የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና የአዋጁን አፈጻጸም ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የቀረበው የማሻሻያ አዋጅ ወቅታዊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የሚስተዋሉ ችግሮችን አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የፍትህ ሚኒስትሯ ሀና አረአያስላሴ በሰጡት ማብራሪያ የማሻሻያ አዋጁ ባለፉት ዓመታት በትግበራ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም