ከደብረ ብርሃን- ደነባ-ለሚ መገጠያና ከደነባ እነዋሪ ጅሁር እየተገነባ ባለው መንገድ የአስፋልት ማንጠፍ ስራ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከደብረ ብርሃን- ደነባ-ለሚ መገጠያና ከደነባ እነዋሪ ጅሁር እየተገነባ ባለው መንገድ የአስፋልት ማንጠፍ ስራ ተጀመረ

ደብረ ብርን፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደብረ ብርሃን-ደነባ-ለሚ መገንጠያና ከደነባ እነዋሪ ጅሁር እየተገነባ ባለው መንገድ የአስፋልት ማንጠፍ ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በአስተዳደሩ የደብረ ብርሃንና አካባቢው ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኢንጅነር ንጋቱ ውድነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
ከዚህም ከደብረ ብርሃን-ደነባ-ለሚ መገጠያና ከደነባ እነዋሪ ጅሁር እየተገነባ ያለው መንገድ 108 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የአስፋልት ኮንክሪት አንዱ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል።
በመንገድ ፕሮጀክቱ ሰሞኑን የአስፋልት ማንጠፍ ስራ መጀመሩን አስታወቀዋል።
የፕሮጀክቱ መገንባት የለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚመረተውን ሲሚንቶ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ የግንባታ ኢንዱስትሪውን እድገት ማፋጠን የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የአርሶ አደሩን ምርት ወደ ከተማ በማውጣትና የኢንዱስትሪ ውጤቶችንም ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ የገበያ ማረጋጋት ስራ ማከናወን እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የመንገዱ ግንባታ ተቋራጭ የሆነው የሰንሻይን ኮንስትራክሽን የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ይታያል ስማቸው በበኩላቸው፤ ሰሞኑን የተጀመረው የአስፋልት ማንጠፍ ስራ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ 20 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከ15 ሜትር እስከ 30 ሜትር ስፋት ያላቸው አምስት ድልድዮች ግንባታ በበጀት ዓመቱ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ የፕሮጀክቱ ቀሪውንም ከፍጻሜ ለማድረስ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
ከደብረ ብርሃን-ደነባ-ለሚ መገጠያና ከደነባ እነዋሪ ጅሁር የመንገድ ፕሮጀክት ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ እንደሚገኝ ተመልክቷል።