ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ሀብት ማሟላት የሚያስችል አቅም እየፈጠረች ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ ሀብት ማሟላት የሚያስችል አቅም እየፈጠረች ነው - አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅ የምታደርገው ጉዞ ስኬታማ መሆኑን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን በራስ ሀብት መቋቋም የሚያስችል አቅም እየፈጠሩ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት እና ተረጂነትን ታሪክ ለማድረግ መግባባት በመፍጠር በዝግጅት፣ በትግበራ እና በማጽናት ምዕራፎች ወደ ተግባር መገባቱን አብራርተዋል፡፡
መንግሥት የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ ለመቀየር ቁጭት መፍጠሩን ገልጸው፥ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ እምቅ ሃብት ያላት ሀገር ናት ያሉት ኮሚሽነሩ፥ ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ የውሃ ሃብትን ጨምሮ በርካታ የተማረ ሰው ሃይል ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡
ይህም ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ማሟላት የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ ግቡን ለማሳካትም ከ20 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ በሁሉም ክልሎች ወደ ትግበራ መገባቱን አንስተዋል።
በግብርናው ዘርፍ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመሩ ሥራዎችን እያገዙ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የዕለት ደራሽና የመጠባበቂያ እህል ክምችትን እንደሚያሳድጉም ነው ያብራሩት።
ኮሚሽነሩ አክለውም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ፖሊሲ ጸድቆ በክልሎች እየተተገበረ ነው ብለዋል።
ተረጂነትን ለማስቀረትና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡