ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩና ዜጎቿን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ ማሻሻያዎች አከናውናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩና ዜጎቿን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የዲፕሎማሲ ማሻሻያዎች አከናውናለች
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡- ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩና ዜጎቿን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዲፕሎማሲያዊ የማሻሻያ ስራዎች ማከናወኗን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲሕ ማሀዲ(ዶ/ር) ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲሕ ማሀዲ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስከብሩና ዜጎቿን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዲፕሎማሲያዊ የማሻሻያ ስራዎች ማከናወኗን ተናግረዋል።
በተከናወኑት ማሻሻያዎች የአሰራር፣ የአደረጃጀት፣ የቴክኖሎጂ፣ የሰው ሃብት ልማት መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን የማስተካከል ስራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።
የተከናወኑት የለውጥ ተግባራት ኢትዮጵያን የሚመጥንና ተሰሚነቷን የሚያሳድግ አደረጃጀት መፍጠር ማስቻሉንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የፕሪቶሪያና የአንካራ ስምምነትን ጨምሮ የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን እንዲፈቱ ያሳየችው ቁርጠኝነት የበሳል ዲፕሎማሲ ውጤት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከራሷ አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚ እንዲያደርግ ታስቦ መቀረጹንም አስታውቀዋል።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን የሁለትዮሽና ባለብዙ ዘርፍ ግንኙነት ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት በዲፕሎማሲው መስክ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን በአብነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በባለ ብዙ ዘርፍ መድረኮች የነበራት ተሳትፎ በብሪክስ አባልነት እንድትመዘገብ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ሃብቷን እንዳትጠቀም የውጭ ጫና ሲደረግባት መቆየቱን አስታውሰው በለውጡ አመታት ዲፕሎማሲውን በመጠቀም ጫናውን መቀልበስ ተችሏል ነው ያሉት።
በተለይም የአባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ እንዲፈረም ኢትዮጵያ ውጤታማ የዲፕሎማሲ አካሔድ መጠቀሟን ጠቅሰው በዋናነት የባሕር በርን በተመለከተ ብሔራዊ ጥቅሟን ባስከበረ መልኩ ጥያቄዋን ማቅረብ መቻሏን አስረድተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው በሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ የተካሔደው ለውጥ ትልቅ ስኬት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።
በዋናነትም ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ የተሄደበት ርቀት ስኬታማ እንደነበርና በተለይም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውጤታማ ስራ መስራት መቻሉንም ተናግረዋል።