ሀገራዊ ለውጡ በክልሉ ሁለንተናዊ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡ በክልሉ ሁለንተናዊ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ዕድል ፈጥሯል
አሶሳ፤መጋቢት 23/2017(ኢዜአ):- ሀገራዊ ለውጡ በክልሉ በርካታ ፖለቲካዊ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ዕድል መፍጠሩን በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር የክልሉን የሰባት ዓመታት የለውጥ ጉዞ አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ኢሳቅ በመግለጫቸው ሀገራዊ ለውጡ ከለውጡ ዓመታት በፊት የነበረውን የፖለቲካ ስብራት የጠገነ እና ሀገራዊ አንድነትን ያላበሰ ፓርቲ እንዲመሰረት ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ክልሉ ራሱን በነፃነት እንዲያስተዳድር ዕድል ያገኘበት፤ በሀገራዊ ጉዳይ ውሳኔ ሰጪ እና እኩል ተሳታፊ እንዲሆን የፖለቲካ አውድ የተፈጠረበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የዴሞክራሲ ልምምዱን ለማጠናከር እና የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማስፋፋትም ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሆነ አቶ ኢሳቅ አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊ እና አካታች መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ ሀገሪቷን ከመበታተን ያዳነ እና የህዝቦችን አብሮነት የሚያጎለብቱ ስራዎችን ያከናወነ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ፓርቲው ፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም በማሻሻል ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከነበረበት ችግር ተላቆ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ አንዱ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የለውጡ መንግስት ተግባራዊ ያደረጋቸው ኢንሼቲቮች በክልሉ ተግባራዊ መሆናቸውን ተናግረው፥ የሌማት ትሩፋት፣አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች የልማት ስራዎች የዜጎችን የኢኮኖሚያዊ አቅም እያሳደጉ ነው ብለዋል።
በቅርብ ዓመታት የተጀመረው ከተሞችን የማስዋብ ስራም ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ እና ይህም የለውጡ መንግሥት ትሩፋት እንደሆነ ጠቁመዋል።
በአሶሳ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ውበት የሚያጎላ እና ለትውልዱ ምቹ ከተማ ለመፍጠር እየተከናወነ ያለ ስራ ነው ብለዋል።
ከለውጡ መንግስት ጋር ተያይዞ በክልሉ የጫካ ትግል አማራጭ ያደረጉ ኃይሎች በሰላማዊ መንገድ ተመልሰው ትጥቅ እንዲፈቱና በልማቱ እንዲሳተፉ የተደረገበት መንገድ ትልቅ ፖለቲካዊ ትርጉም የሚሰጠው እንደሆነም አክለዋል።
የሰላም ተመላሾችም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሰማሩ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።