ቀጥታ፡

በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎትን 92 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ ተችሏል

ጋምቤላ፤መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የጤና መድህን አገልግሎትን 92 ነጥብ 8 በመቶ ማድረስ መቻሉን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ጸጋዬ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የጤና መድህን አገልግሎቱን በክልሉ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በዚህም በክልሉ ከሚገኙ አስራ አራት ወረዳዎች መካከል በአስራ ሶስቱ ወረዳዎች የጤና መድን አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸው ይህም የክልሉን የጤና መድህን ሽፋን ወደ 92 ነጥብ 8 በመቶ ሸፍኗል ብለዋል፡፡

የጤና መድህን ፕሮግራሙ ገቢን መሠረት ያደረገ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ በመደረጉ ዜጎች እንደየ አቅማቸው የጤና መድህን አገልግሎሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ24 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል አቶ ኡፓዲ አኳይ በሰጡት አስተያት የጤና መድህን ፕሮግራሙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።

የጤና መድህን አባል ከሆኑ ወዲህ የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በወቅቱ በመክፈል እራሳቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ያለምንም ተጨማሪ ወጪ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙም አቶ ኡፓዲ ገልጸዋል፡፡

የጤና መድህን አባል ከሆኑ ወዲህ ነፃ ህክምናና መድኃኒት በማግኘታቸው ጤናቸው መሻሻሉን የገለጹት ደግሞ በጋምቤላ አጠቃላይ ሆስፒታል የስኳር በሽታ ህክምናቸውን ሲከታተሉ ያገኘናቸው ወይዘሮ አይናለም ተርፋ ናቸው፡፡

ሌለው አስተያየት ሰጪ አቶ ጋዴድ ቾል በሰጡት አስተያየት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆናቸው የህክምና ወጪ ሳያሳስባቸው ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በነጻ እያሳከሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም