ቀጥታ፡

የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለተነደፉ ፖሊሲዎች ስኬታማነት የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል

ሐመር-ዲመካ፤መጋቢት 23/2027 (ኢዜአ)፦መንግስት የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ለተነደፉ ፖሊሲዎች ስኬታማነት ድጋፉን እንደሚያጠናክር የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን አስታወቀ፡፡

ፋውንዴሽኑ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች እየተገበረ በሚገኘው የወጣቶች የራስ ስራ ፈጠራ ፕሮጀክት የ11 ወራት የስራ እንቅስቃሴን አስመልክቶ በዲመካ ከተማ እየመከረ ነው።

የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ እንደገለጹት፥ መንግስት የወጣቱን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የቀረፃቸው ፖሊሲዎች ውጤት እያመጡ መሆኑንና ከወጣቶች ቁጥር አኳያ ግን ብዙ መስራት ይጠበቃል።

የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽንም የወጣቱን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት እየተገበራቸው ያሉ ፖሊሲዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በፋውንዴሽኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተኮር ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሙያ በፍቃዱ ኢሳያስ (ዶ/ር)፥ፋውንዴሽኑ በዞኖቹ በተመረጡ ወረዳዎች ለ3 ዓመታት የሚቆይ የወጣቶች የራስ ስራ ፈጠራ ፕሮጀክት ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በ2016 ዓ/ም የተጀመረ መሆኑን ገልፀው፥ በሶስት ዓመታት ጊዜ ውስጥም ከ32 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በአስተሳሰብ ቅኝት፣ በቢዝነስ ክህሎት ማጎልበት ስራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ የመጀመሪያው 11 ወራት ከ16 ሺህ 700 በላይ ወጣቶች በ641 ኢንተርፕራይዞችና በ138 ህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተውና የክህሎት ስልጠና አግኝተው ወደ ተግባር መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣በእንስሳት እርባታ፣ በኢኮ ቱሪዝምና በሌሎች ቢዝነስ ተኮር ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልፀው መንግስት የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን በማዘጋጀት ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማሊኮ የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን በዞኑ በርካታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።

በዞኑ በርካታ ፀጋዎችና ሀብቶች እንዳሉ አንስተው፥ አምራቹን ኃይል በመጠቀም እነዚህን ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚ ምንጭነት ለመለወጥ የተጀመረውን ጥረት ፋውንዴሽኑ እያገዘ ነው ብለዋል፡፡

ወጣቱ ተግባር ተኮር የክህሎት ስልጠና በማግኘት በገቢ ማመንጫ ስራዎች ላይ እንዲሰማራና የሀብት ባለቤት እንዲሆን ፋውንዴሽኑ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም