የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤መጋቢት 23/2017(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ዛሬ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ጨረታው ባንኩ በየሁለት ሳምንት መደበኛ እና ተከታታይ የሚያካሂደው የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ አካል መሆኑን ገልጿል።
በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ብቸኛው የወርቅ ገዥ ለሆነው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንደሆነና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከተገመተው በላይ እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሷል።
ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አንጻር ባንኩ በቀጣይ ወራት በመደበኛነት በየሁለት ሳምንቱ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታዎችን ለማካሄድ መወሰኑን ነው ባንኩ ያስታወቀው።
ይህ አካሄድ በማዕከላዊ ባንክ እየተከማቸ ካለው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን መጠን ለግሉ ዘርፍ ለማቅረብና የባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት እንደሚረዳ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት የሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋትና ሪፎርሙ ከተጀመረ ወዲህ መሻሻል እያሳየ የመጣውን የውጭ ክፍያ ሚዛን በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡
በዚሁ መሰረት ዛሬ የ50 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ይካሄዳል።
ባንኮች በጨረታው ላይ በስፋት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።