ቀጥታ፡

የግብርና ፍኖተ ካርታው በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው

አሶሳ፤መጋቢት 23/2017(ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ፍኖተ ካርታው በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ።

የግብርና ፍኖተ ካርታ ወደ ትግበራ እንዲገባም የዘርፉ የምርምር ተቋማት እና የመንግስት አካላት በቅንጅት መስራት ተገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ፍኖተ ካርታ ዐቢይ እና ቴክኒክ ኮሚቴዎች በቀጣይ በሚከናወኑ ስራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አሻድሊ ሀሰን፥ፍኖተ ካርታው በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ጠቅሰው፤በተመረጡ የሰብል ዓይነቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል ብለዋል።

ክልሉ ለግብርና ስራ አመቺ በመሆኑ ፍኖተ ካርታው ስራውን የበለጠ ለማስፋት እና ምርታማነትን ለመጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አንስተዋል።

ህብረተሰቡ የፍኖተ ካርታውን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ለማድረግ በቀጣይ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)፥ ክልሉ ፍኖተ ካርታውን ወደ ተግባር ለመቀየር እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ ፍኖተ ካርታው ለክልሉ አየር ፀባይ ተስማሚ እንዲሁም ለምግብ ዋስትና ተመራጭ የሆኑ የሰብል አይነቶችን በስፋት በማምረት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያግዛል።

በተጨማሪም የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በተደራጀ መልኩ በማምረት ሁሉን አቀፍ ምርታማነት ለማሳደግ ፍኖተ ካርታው የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም