ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል የፋይናንስ ስምምነቶች ተፈራረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ለማሳደግ የሚያስችል የፋይናንስ ስምምነቶች ተፈራረመች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ማሳደግን ያለመ ሁለት የፋይናንስ ስምምነቶች ተፈራርማለች።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም ናቸው ፡፡
አጠቃላይ ስምምነቱ የ96 ነጥብ 367 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ከተፈረመው ስምምነት ውስጥ 50 የአሜሪካን ዶላሩ ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር በብድር መልክ የተገኘ ነው።
ቀሪው 46 ነጥብ 367 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከዓለም አቀፉ የትምህርት አጋርነት ፈንድ በድጋፍ የተገኘ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ብድሩ እና ድጋፋ የኢትዮጵያ መንግስት የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን እኩል ተደራሽነት ለማሳደግ እና የትምህርት ውጤት ለማሻሻል እያከናወነ ላለው ስራ እንደሚውል ተገልጿል።
ስምምነቶቹ ኢትዮጵያ የትምህርትን ጥራትን ለማሻሻል በተለይም የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ለማሻሻል ያላትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።
ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የያዘው ስትራቴጂ አካል መሆኑን ገልጿል።