በብሄራዊ ጉዳዮች በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ልዕልና የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
በብሄራዊ ጉዳዮች በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ልዕልና የሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ እንሰራለን
ሚዛን አማን፤መጋቢት 23/2017 (ኢዜአ)፦በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመቆም እሳቤ በመያዝ የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ እንደሚረባረቡ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ፓርቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ፤በፖለቲካው የተለያየ እሳቤ ቢኖረንም አንድ ሀገርና አንድ ሕዝብ ነው ያለን ብለዋል።
አቶ ወንድሙ አክለውም የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ ሳንደራደር በመቆም በጋራ መሥራት ይጠበቅብናልብለዋል።
በዚህ እይታ መንግሥት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በጋራ ምክር ቤት ተገናኝተን ሀሳባችንን በመጋራት ጭምር እያደረግን ያለውን ተሳትፎ እናጠናክራለን ሲሉም ገልጸዋል።
በተለይም የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የሕዝብ የሆኑ የልማት ሥራዎች ጥራታቸው ተጠብቆ ተገንብተው ለአገልግሎት እንዲበቁ፣የእኛ ነው በሚል እሳቤ ክትትል በማድረግ እየሠራን ነው ያሉት ደግሞ ከእናት ፓርቲ አቶ ወንድማገኝ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።
እንደ ሀገር የተሻለ የፖለቲካ ሥነ ምሕዳር፣የተሻለ ልማትና መረጋጋት እንዲፈጠር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን ጠቃሚ ተግባራትን በጋራ እናስቀጥላለን ብለዋል።
ከተናጠል ሩጫ ይልቅ በጋራ እየተደማመጡ የመንቀሳቀስ ፖለቲካዊ ባህል በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ዳብሮ መቀጠል አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎቸ የጋራ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰሎሞን አየለ ፓርቲዎች ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርጉ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በገንዘብና በሀሳብ የመደገፍ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በሀገራዊ እድገት ጉዳይ፣በሰላም እና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ልዩነት ሊፈጠር እንደማይገባም በአጽንኦት ተናግረዋል።
ከተባበርን ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንችላለን ያሉት አቶ ሰሎሞን በአንጻሩ የልዩነት እሳቤዎችን ብቻ ይዞ መንቀሳቀስ ማንንም የማይጠቅም መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ተረድቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ትናንት በሚዛን አማን ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።